2 Samuel 11

ዳዊትና ቤርሳቤህ

1ነገሥታት ለጦርነት በሚወጡበት፣ በጸደይ ወራት ዳዊት ኢዮአብን ከንጉሡ ሰዎችና ከመላው የእስራኤል ሰራዊት ጋር አዘመተው፤ እነርሱም አሞናውያንን አጠፉ፤ ረባት የተባለችውንም ከተማ ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።

2አንድ ቀን ማታ፣ ዳዊት ከዐልጋው ተነሥቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ ከሰገነቱ ላይ እንዳለም፣ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ በጣም ውብ ነበረች። 3ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ አጠያየቀ። ሰውየውም፣ “ይህች የኤልያብ ልጅ፣ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለ። 4ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ እርሱ ወዳለበት ገባች፤ አብሯትም ተኛ። በዚህም ጊዜ ወርኃዊ የመንጻት ጊዜዋን ፈጽማ ነበር። ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች። 5ሴቲቱ ፀነሰች፤ ለዳዊትም፣ “አርግዣለሁ” ብላ ላከችበት።

6ስለዚህም ዳዊት ለኢዮአብ፣ “ኬጢያዊውን ኦርዮን ወደ እኔ ስደደው” ሲል ላከበት፤ ኢዮአብም ወደ ዳዊት ላከው። 7ኦርዮን በመጣ ጊዜም፣ ዳዊት የኢዮአብንና የሰራዊቱን ሁሉ ደኅንነት እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው። 8ከዚያም ዳዊት ኦርዮን፣ “በል እንግዲህ ወደ ቤትህ ወርደህ እግርህን ታጠብ” አለው። ኦርዮን ከቤተ መንግሥት ተሰናብቶ ወጣ፤ ንጉሡም ማለፊያ ምግብ አስከትሎ ላከለት። 9ነገር ግን ኦርዮ ከጌታው አገልጋዮች ሁሉ ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጽር በር ተኛ እንጂ፣ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር።

10ዳዊት፣ “ኦርዮን ወደ ቤቱ አልሄደም” መባሉን ሲሰማ ኦርዮን፣ “ከመንገድ ገና አሁን መግባትህ አይደለምን? ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

11ኦርዮም ዳዊትን፣ “ታቦቱ፣ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፣ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ሰዎች አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረው፣ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? እንዲህ ያለውን ነገር እንደማላደርገው በነፍስህ እምላለሁ” አለው።

12ከዚያም ዳዊት፣ “እንግዲያውስ ዛሬ እዚህ ዕደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። ስለዚህ ኦርዮን በዚያ ዕለትና በማግስቱም እዚያው ኢየሩሳሌም ቈየ። 13በማግስቱም ዳዊት ራሱ ባለበት ግብዣ አድርጎለት በላ፤ ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ሲመሽም ኦርዮን በምንጣፉ ላይ ለመተኛት የጌታው አሽከሮች ወዳሉበት ወጥቶ ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም።

14ሲነጋም ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮን እጅ ላከለት፤ 15በደብዳቤውም ላይ፣ “ኦርዮ ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ።

16ስለዚህም ኢዮአብ ከተማዪቱን በከበባት ጊዜ፣ እጅግ ጠንካራ ተከላካዮች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር ኦርዮን መደበው። 17የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከዳዊት ሰራዊት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደቁ፤ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።

18ኢዮአብም በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ። 19መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፣ 20ንጉሡ በቍጣ ቱግ ብሎ ‘ለመዋጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለ ምንድን ነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰድዱባችሁ አታውቁም ኖሯል? 21የይሩቤሼትን
ጌዴዎን፣ ይሩበአል በመባልም ይታወቃል።
ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤስ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቅቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በማለት ቢጠይቅህ፣ አንተም መልሰህ፣ ‘አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞቷል’ ብለህ ንገረው።”

22ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደ ደረሰም፣ ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው። 23መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፤ “ሰዎቹ ዐየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወጥተው እስከ ሜዳው ድረስ መጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማዪቱ ቅጽር መግቢያ ድረስ አሳድደን መለስናቸው። 24ከዚያም ባለ ፍላጻዎቹ ከግንቡ ላይ ሆነው በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ስለ ለቀቁ፣ ከንጉሡ አገልጋዮች ጥቂቶቹን ገደሉ፤ አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።”

25ዳዊትም፣ መልእክተኛውን፣ “እንግዲህ እንዲህ ብለህ ይህን ለኢዮአብ ንገረው፤ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፣ ሌላ ጊዜም ሌላውን ትበላለችና በዚህ አትዘን’ ” አለው።

26የኦርዮን ሚስት ባሏ መሞቱን በሰማች ጊዜ ዐዘነች፤ አለቀሰችለትም። 27የሐዘኑ ጊዜ ካበቃ በኋላም፣ ዳዊት ልኮ ቤርሳቤህን ወደ ቤቱ አስመጣት፤ ሚስቱ ሆነች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት የሠራው ሥራ እግዚአብሔርን አላስደሰተውም ነበር።

Copyright information for AmhNASV